Luke 6

የሰንበት ጌታ

6፥1-11 ተጓ ምብ – ማቴ 12፥1-14፤ ማር 2፥23–3፥6 1በአንድ የሰንበት ቀን ኢየሱስ በዕርሻ መካከል ያልፍ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም እሸት ቀጥፈው በእጃቸው እያሹ ይበሉ ነበር። 2ከፈሪሳውያን መካከል አንዳንዶቹ ግን፣ “በሰንበት ቀን ሊደረግ ያልተፈቀደውን ለምን ታደርጋላችሁ?” አሏቸው።

3ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ዳዊት በተራበ ጊዜ ከባልንጀሮቹ ጋር ያደረገውን ከቶ አላነበባችሁምን? 4ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ለካህናት ብቻ የተፈቀደውን ኅብስተ ገጽ ወስዶ በላ፤ አብረውት ለነበሩትም ሰጣቸው።” 5ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ለሰንበት ጌታዋ ነው” አላቸው።

6በሌላ ሰንበት ቀንም ወደ ምኵራብ ገብቶ ያስተምር ነበር፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ አንድ ሰው ነበረ። 7ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም ሊከስሱት ምክንያት በመፈለግ፣ ይፈውሰው እንደ ሆነ ለማየት ይጠባበቁት ነበር። 8ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እጁ የሰለለውን ሰው፣ “ተነሥተህ በመካከል ቁም” አለው፤ ሰውየውም ተነሥቶ ቆመ።

9ኢየሱስም፣ “እስቲ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ፤ በሰንበት ቀን የተፈቀደው በጎ ማድረግ ነው ወይስ ክፉ ማድረግ? ነፍስ ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው።

10ደግሞም ኢየሱስ በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየውም እንደ ተባለው አደረገ፤ እጁም ፈጽሞ ዳነለት። 11ሰዎቹ ግን በቍጣ ተሞሉ፤ በኢየሱስ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸውም እርስ በርስ ተወያዩ።

የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መመረጥ

6፥13-16 ተጓ ምብ – ማቴ 10፥2-4፤ ማር 3፥16-19፤ ሐሥ 1፥13 12ከእነዚያም ቀናት በአንዱ ኢየሱስ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ ዐደረ። 13ሲነጋም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ ከእነርሱ ዐሥራ ሁለቱን መረጠ፤ እነዚህንም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤ 14እነርሱም፣ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ፊልጶስ፣ በርተሎሜዎስ፣ 15ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ቀናተኛ የተባለው ስምዖን፣ 16የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ኋላ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነበሩ።

የቡራኬና የወዮታ ስብከት

6፥20-23 ተጓ ምብ – ማቴ 5፥3-12 17ኢየሱስም አብሯቸው ከተራራው ወርዶ ደልዳላ ቦታ ላይ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም እጅግ ብዙ ሰዎች በዚያ ነበሩ፤ ከይሁዳ ሁሉና ከኢየሩሳሌም እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ጠረፍ የመጣ ብዙ ሕዝብም በዚያ ነበረ፤ 18እነዚህም የመጡት ሊሰሙትና ካለባቸው ደዌ ሊፈወሱ ነበር። በርኩሳን
ወይም ክፉ
መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩትም ተፈወሱ፤
19ኀይል ከእርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር፣ ሰዎቹ ሁሉ እርሱን ለመንካት ይፈልጉ ነበር።

20ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመመልከት እንዲህ አለ፤

“እናንት ድኾች ብፁዓን ናችሁ፤
የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና፤
21 እናንት አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፤
ኋላ ትጠግባላችሁና፤
እናንት አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፤
ኋላ ትሥቃላችሁና፤
22 ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሏችሁ፣
ከመካከላቸው ሲለዩአችሁና ሲነቅፏችሁ፣
ክፉ ስምም ሲሰጧችሁ ብፁዓን ናችሁ።
23 “እነሆ፤ ወሮታችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፣ በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ፤ ፈንድቁም፤ የቀድሞ አባቶቻቸውም በነቢያት ላይ ያደረጉት ይህንኑ ነበርና።

24 “ነገር ግን እናንት ሀብታሞች ወዮላችሁ፤
መጽናናታችሁን አሁኑኑ ተቀብላችኋልና።
25 እናንት አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፤
ኋላ ትራባላችሁና።
እናንት አሁን የምትሥቁ ወዮላችሁ፤
ኋላ ታዝናላችሁ፤ ታለቅሳላችሁም።
26 ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም
ሲናገሩላችሁ ወዮላችሁ፤
የቀድሞ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች
ነቢያት ያደረጉላቸው ይህንኑ ነበርና።

ጠላትን መውደድ

6፥29፡30 ተጓ ምብ – ማቴ 5፥39-42 27 “ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፤ 28የሚረግሟችሁን መርቁ፤ ለሚበድሏችሁም ጸልዩ። 29አንዱን ጕንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጕንጭህን ደግሞ ስጠው፤ መጐናጸፊያህን ለሚወስድብህ እጀ ጠባብህን አትከልክለው። 30ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤ ንብረትህን የሚወስድ እንዲመልስልህ አትጠይቀው። 31ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው።

32 “የሚወድዷችሁን ብትወድዱ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ የሚወድዷቸውን ይወድዳሉና። 33መልካም ላደረጉላችሁ መልካም ብታደርጉ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ እንደዚያ ያደርጋሉና። 34ብድር ይመልሳል ለምትሉት ብታበድሩ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ ያበደሩትን ያህል መልሰው ለመቀበል ለኀጢአተኞች ያበድራሉ። 35ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ መልሳችሁ ለመቀበል ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፤ በዚህም ወሮታችሁ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ቸር ነውና። 36አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ እናንተም ርኅሩኆች ሁኑ።

በሌሎች አለመፍረድ

6፥37-42 ተጓ ምብ – ማቴ 7፥1-5 37 “አትፍረዱ፤ አይፈረድባችሁም፤ አትኰንኑ፤ አትኰነኑም። ይቅር በሉ፤ ይቅር ትባላላችሁ። 38ስጡ፤ ይሰጣችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ስለሚሰፈርላችሁ፣ ጫን በተደረገ፣ በተነቀነቀና በተትረፈረፈ መልካም መስፈሪያ ተሰፍሮ በዕቅፋችሁ ይሰጣችኋል።”

39ደግሞም ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱ ተያይዘው ጕድጓድ አይገቡምን? 40ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ነገር ግን በሚገባ የተማረ ሰው ሁሉ እንደ መምህሩ ይሆናል።

41 “በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጕድፍ ለምን ታያለህ? በራስህ ዐይን ውስጥ የተጋደመውን ግንድ አትመለከትምን? 42በራስህ ዐይን ውስጥ ያለውን ግንድ ሳታይ ወንድምህን፣ ‘ወንድሜ ሆይ፤ በዐይንህ ውስጥ ያለውን ጕድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ልትለው ትችላለህ? አንተ ግብዝ፤ በመጀመሪያ በዐይንህ ውስጥ የተጋደመውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያ በኋላ በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጕድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ።

ዛፍና ፍሬው

6፥43፡44 ተጓ ምብ – ማቴ 7፥16፡18፡20 43 “መልካም ዛፍ ሆኖ ሳለ መጥፎ ፍሬ የሚያፈራ የለም፤ እንዲሁም መጥፎ ዛፍ ሆኖ መልካም ፍሬ የሚያፈራ የለም። 44ዛፍ ሁሉ በፍሬው ይታወቃል፤ ከእሾኽ የበለስ ፍሬ አይለቀምም፤ ከቀጋ ቍጥቋጦ የወይን ፍሬ አይቈረጥም። 45መልካም ሰው በልቡ ከሞላው መልካም ነገር መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ከሞላው ክፉ ነገር ክፉውን ያወጣል፤ ሰው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን በአፉ ይናገራልና።

ልባምና ሰነፍ ቤተ ሠሪዎች

6፥47-49 ተጓ ምብ – ማቴ 7፥24-27 46 “እኔ የምለውን አታደርጉም፤ ታዲያ ለምን፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ’ ትሉኛላችሁ? 47ወደ እኔ የሚመጣ፣ ቃሌንም ሰምቶ የሚፈጽም ሁሉ ማንን እንደሚመስል ላሳያችሁ፤ 48ቤት ለመሥራት አጥልቆ የቈፈረና በዐለት ላይ መሠረቱን የመሠረተ ሰው ይመስላል፤ ጐርፍ በመጣ ጊዜ የውሃው ሙላት ያን ቤት ገፋው፤ በሚገባ ስለ ታነጸም ሊያነቃንቀው አልቻለም። 49ቃሌን ሰምቶ የማይፈጽም ግን ቤቱን ያለ መሠረት በዐፈር ላይ የሠራን ሰው ይመስላል፤ የወንዝ ሙላትም ቤቱን በመታው ጊዜ ወዲያው ወደቀ፤ ክፉኛም ፈራረሰ።”

Copyright information for AmhNASV